Thursday, September 3, 2015

በእስር ላይ የሚገኙ ሦስት የሰማያዊ አባላት በዓለም ላይ ከተመረጡ 20 የፖለቲካ እስረኞች መካከል ተካተቱ

ሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች የአንድ ወር ዘመቻ ያደርጉላቸዋል

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር


በአሜሪካ መንግስት ኦፊሳላዊ ድረ ገጽ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አስተባባሪነት በዓለም ላይ ለተመረጡ 20 ሴት የፖለቲካ እስረኞች ለአንድ ወር የሚቆይ ዘመቻና ማስታወሻ ሊደረግላቸው ነው፡፡ ከ20ዎቹ ሴት የፖለቲካ እስረኞች መካከል ሦስቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ሁሉም የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ናቸው፡፡

ከዛሬ 20 አመት በፊት ሴቶችን ለማብቃት፣ የጾታ እኩልነትን ለማስፈን እና የልጃ ገረዶችን ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅ የቤጂንግ መርሃ ጉዞ ተቀምጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በእነዚህ 20 አመታት ልክ ከዓለም ሀገራት በፖለቲካ እስረኝነታቸው የተመረጡ 20 ሴት እስረኞችን ለማሰብ የሚደረገው ዘመቻ መነሻው ይህ መርሃ ጉዞ ነው፡፡

በዚህ መሰረት ከኢትዮጵያ ብሌን መስፍን፣ ንግስት ወንዲፍራው እና ሜሮን አለማየሁ የተካተቱ ሲሆን ከቻይና እንዲሁ ሦስት ሴት የፖለቲካ እስረኞች ተመርጠው ይታወሳሉ፡፡ ከብዙ ሴት የፖለቲካ እስረኞች መካከል እነዚህ ጥቂቶች መሆናቸውን የጠቀሰው ድረ ገጹ በመስከረም ወር ‹‹ሴቶችን አብቋቸው፣ አትሰሯቸው!›› በሚል መርህ ዘመቻው ይደረጋል፡፡ በዚህም መንግስታት ሴቶችን በፖለቲካ አመለካከታቸው ማሰር አቁመው ማብቃት ላይ እንዲያተኩሩ መልዕክት ይተላለፍበታል፡፡


በሌላ በኩል ደግሞ ዘመቻው ለታሳሪ ቤተሰቦችና ለራሳቸው ለታሳሪዎች ብቻቸውን እንዳልሆኑና እንዳልተዘነጉ ለማሳየት ታስቦ እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡


በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ የሰጡት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ በኢትዮጵያ ሦስት ሴት የፖለቲካ እስረኞች በዚህ ደረጃ መጠቀሳቸው በሀገራችን ያለውን ስርዓት ዓለም እንደተረዳውና ኢትዮጵያ በመጥፎ እንድትነሳ እያደረጋት መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡


ዘመቻው እንዲደረግላቸው ከተመረጡት መካከል ከኢትዮጵያና ቻይና ሶስት ሶስት፣ ከቬትናም፣ አዘርባጃንና በርማ ሁለት ሁለት እንዲሁም ከኢራን፣ ግብፅ፣ ኤርትራ፣ ኡዝቤኪስታን፣ ቬንዞዌላ፣ ሶሪያ፣ ሩሲያ/ዩክሬንና ሰሜን ኮሪያ አንድ አንድ ሴት የህሊና እስረኞች ናቸው፡፡


http://www.zehabesha.com/amharic/archives/46394

No comments:

Post a Comment